"ሚስቴ በስራ ምክንያት ከከተማ እንደወጣሁ ነው የምታውቀው። በእንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ ተደብቄ ወደ መኝታ ክፍላችን ምርጡን ጓደኛዬን ስትወስደው እያየኋት እንደነበር የገባት ከረፈደ ነው።"

መሳጭ እውነተኛ አጭር ታሪክ | ዴቪድ ዊሊያም | ትርጉም አ.በ


ስሜ ዳዊት ይባላል። 35 አመቴ ነው። በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ በአርክቴክትነት እሰራለሁ። ስራዬ ቤቶችን ዲዛይን ማድረግ ነው። ወረቀቶችና ኮምፒውተሮች ላይ ላይ መስመሮችን አሰምራለሁ፣ እና እነዚህ መስመሮች ግድግዳዎች ይሆናሉ። ጣራዎች ይሆናሉ። ሰዎች ደስተኛ እና ደህና ሆነው የሚኖሩባቸው ቤቶች ይሆናሉ።

ለሰባት አመታት፣ የራሴን ጥሩ ቤት ዲዛይን አድርጌያለሁ ብዬ አስብ ነበር።

የምወዳት ሚስት አለችኝ። ሳራ ትባላለች። እሷን ሳያት የወደፊት ህይወቴ ይታየኛል። ረጅምና ጥቁር ለስላሳ ፀጉር አላት። ፈገግታዋ በብርድ ጊዜ እንኳን ያሞቃል። የተገናኘነው ሁለታችንም የ25 አመት ወጣቶች በነበርንበት ጊዜ ነበር። ያኔ ኑሯችንን አንደላቆ የሚያኖር ገንዘብ አልነበረንም። የምንበላው ርካሽ ምግቦችን ነበር። ህልማችን ግን ትልቅ ነበር። አሁንን የለንን ህይወት ደረጃ በደረጃ ነው የገነባነው።

የእኔ ጠንክሮ መስራት ጊዜውን ጠብቆ ከፈለን። ከሀለት አመት በፊት ቆንጆ ቤት ገዛን። ቤታችን ከመንገድ ዳር ሆኖ ዙሪያውን ከከበቡት ዛፎች ጎልቶ ይታያል። ሳራ በተከለቻቸው አበቦች የደመቀ ትልቅ ግቢ አለው።  በግቢው ጀርባ ደግሞ በቁጥቋጦዎች የተሸፈነ አነስተኛ የእንግዳ ማረፊያ ቤት አለ።

ይህንን ቤት የሰራሁት ቤተሰቦቼ ሲመጡ ማረፊያ ይሆናቸዋል ብዬ ነበር። ይህንን ቤት የሰራሁት ለጓደኞቼ ማረፊያ ይሆናል ብዬ ነበር። ነገር ግን አንድ ቀን ይህ ቤት የእኔ እስር ቤት ይሆናል ብዬ በፍፁም አስቤ አላውቅም። ህይወቴ ብትንትኑ ሲወጣ እመለከትበታለሁ ብዬ አንድም ቀን ገምቼ አላውቅም ነበር።

ህይወታችን ጥሩ ነበር። አዎ። ወይም እኔ እንደዛ ነበር የማምነው። ረጅም ሰዓታትን በስራ አሳልፋለሁ። የቤቱን ቀሪ ክፍያ ለመክፈል፣ ለሳራ ጥሩ መኪና ለመግዛት፣ እና እሷን ጥሩ መዝናኛ ቦታ ለመውሰድ።

ግን ከስድስት ወራት በፊት ጀምሮ፣ በቤታችን የሚነፍሰው አየር መለዋወጥ ጀመረ። አየሩ የሚያስጠላና ቀዝቃዛ ነበር። ይህ ቅዝቃዜበትናንሽ ነገሮች ነበር የጀመረው። በትናንሽ ዝምታዎች።

ከቢሮ ደክሞኝ ወደ ቤት እመጣ ነበር። እና ወደ ቤት እንደገባሁ "እንዴት ነሽ ማሬ? ውሎ እንዴት ነበር?" ስል እጠይቃታለሁ። ቀና ብላ ታየኛለች። ግን በደንብ አትመለከተኝም። አይኖቿ ባዶ ነበሩ። ምንም የመፈቅ ስሜት አይታይባቸውም። "ደህና" ትላለች። "ራት ስቶቩ ላይ አለ።" ከዚያም ወደ ስልኳ ትመለከታለች።

ከእኔ በላይ ስልኳ ምርጥ ጓደኛዋ መሆን ጀመረ። ሁሌም ከእጇ ላይ አይጠፋም። ወደ ሽንት ቤት ስትሔድ ይዛው ትሔዳለች። ወደ ማብሰያ ክፍል ስትሔድ ይዛው ትሔዳለች። ስትተኛ እንኳን ከትራሷ ስር አርጋው ነው። እኔ መንቀሳቀስ ስጀምርና ወደ እሷ የምቀርብ መስሎ ከተሰማት ወዲያውኑ የስልኳን ስክሪን ታጠፋዋለች።

አንድ ቀን ምሽት ላይ "ከማን ጋር ነው የምታወሪው?" ስል ጠየኳት።

"አይ ከስራ ጋር የተገናኙ ኢሜይሌችን እያየሁ ነው። ዳዊት ብዙ ጥያቄዎችን እየጠየከኝ ነው።" አለችኝ። ከዚያም ሳቀች። ግን ሳቋ ከአንገት በላይ ነበር።

ላምናት ሞከርኩ። ትዳር በእምነት ላይ ነው የሚገነባው አይደል? "ምናልባት በስራ ብዛት ተጨናንቃ ሊሆን ይችላል። ምናልባት ደክሟት ሊሆን ይችላል።" አልኩት ራሴን። ግን በውስጤ የተፈጠረው ስሜት አልጠፋ አለ። በጣም ከባድ ስሜት፣ ልክ እንደ ድንጋይ ሆኖ አንጀቴ ላይ የተቀመጠ መሰለኝ።

ሳራ አዳዲስ ልብሶችን መግዛት ጀመረች። እንደከዚህ ቀደም እንደምትለብሳቸው አይነት ለአይን የማይጎረብጡ ምቹ ልብሶች አልነበሩም። ጭኗን በደንብ የሚያሳዩ አጫጭር ቀሚሶች ነበሩ። ቀይ የከንፈር ቀለሞችን በብዛት ገዛች። ጂም መስራት ጀመረች። እሷ እንደምትለው ጂም የጀመረችው ራሷን ሸንቃጣ ማድረግ ፈልጋ እንደሆነ ነው። ሁሌም ምሽት ላይ ወደ ጁም ትሔዳለች። እና አንዳንድ ጊዜ ቶሎ ወደ ቤት አትመለስም። እስከ ምሽት አራት ሰዓት ድረስ የምትቆይባቸው ቀናቶች ተበራከቱ።

ዘግይታ በምትመጣባቸው ቀናቶች "የዛሬ ስፖርት በጣም ረጅም ነበር።" ትላለች። "ከጂም እንደወጣሁ ሳውና ወሰድኩኝ። ለዛ ነው የቆየሁት።" 

አንድ ቀን ከጁም እንደተመለሰች "ጂም ከጀመርሽ በኋላ ልክ እንደ ወንድ ነው የምትሸቺው" አልኳት በቀልድ መልክ። ግን የእውነቴን ነበር። 

ደነገጠች። ፊቷ ገረጣ። "ዴቭ የጂሙ ሽታ ነው ነዋ። ታውቃለህ ጂም ውስጥ ብዙ ወንዶች አብረውን ይሰራሉ። ሽታው የሁሉም ስፖርተኛ ድብልቅ ነው።"

እንደበፊቱ አቅፋኝ ሰላም ማለቷን አቆመች። እጆቼን መያዝ አቆመች። በምንተኛበት ጊዜ ጀርባዋን ወደእኔ አዙራ መተኛት ጀመረች። በመካከላችን የሆነ ግንብ እየተፈጠረ እንዳለ ተሰማኝ። የማይታይ ግን እኔን ከእሷ የሚጋርድ። በቤቴ ውስጥ ብቸኝነት ተሰማኝ። አጠገቤ ከምታድረው ሴት ጋር ልክ እንደ እንግዳ መተያየት ጀመረን። 

በአንድ ሰኞ ቀን ጠዋት ላይ ግን የመጨረሻው መጀመርያ ጀመረ። 

አለቃዬ ወደ ቢሮው እንድመጣ አስጠራኝ። የተጨነቀ ይመስላል። በእጁ የሆነ ፋይል ይዟል። "ዳዊት" አለ። "በቺካጎ የጀመርነው ትልቅ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ችግር ገጥሞናል። ደንበኛችን ደስተኛ አይደለም። በዚህ ሳምንት ውስጥ ምናልባት ወደዛ ልትሄድ ትችላለህ።"

መስማት የማልፈልገው ዜና ነበር። "በዚህ ሳምንት? ይህ ወር የጋብቻ አመታችንን የምናከብርበት ወር ነው። ሌላ ቀን መሆን አይችልም?" 

"አዝናለሁ ዳዊት" አለ አለቃዬ። "እስካሁን የመሔድህ ጉዳይ አልተረጋገጠም። ግን እባክህ ፕሮግራምህን ክፍት አርገህ ጠብቅ። ሐሙስ ሁሉንም ነገር አሳውቅሃለሁ።" 

ያን ቀን ማታ ራት እየበላን ነበር። እና ነገርኳት። ።

"ማሬ" አልኳት። "አለቃዬ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለአንድ አስቸኳይ ስራ ወደ ቺካጎ ልሄድ እንደምችል አሳውቆኛል። ምናልባት ከሐሙስ እስከ እሁድ ባሉት ቀናት ውስጥ። ግን እስካሁን የመሔዴ ነገር አልተረጋገጠም።" 

በፊት በፊት ሳራ በሳምንቱ መጨረሻ ስራ የምሔድ ከሆነ በጣም ትናደድ ነበር። እና ሁልጊዜ " ዴቭ፣ አብረን የምናሳልፈው ጊዜ ሊኖር ይገባል። ስራ በጣም እያበዛህ ነው።" ትለኝ ነበር። 

ግን አሁን ስነግራት መብላቷን አቆመች። የምትበላበትን የሹካ ማንኪያ አስቀመጠች። አየችኝ። አይኖቿ ግን ንዴት አይታይባቸውም። እያሰቡ ነበር። የሆነ ስሌት የሚያሰሉ ይመስሉ ነበር። 

"ኦው " አለች ዝቅ ባለ ድምፅ። ብርጭቆውን አንስታ አንድ ጉንጭ ውሃ ተጎነጨች። "ጥሩ፣ ስራ በጣም አስፈላጊ ነው ዴቭ። መሄድ ካለብህ መሄድ አለብህ።"

እስከመቼ እንደምቆይ አልጠየቀችኝም። ስለ በረራዬ አልጠየቀችኝም። በቃ እራቷን ወደ መብላት ተመለሰች። ከዛ በኋላ አላውቅም። ግን በጭንቅላቷ የሆነ እቅድ ማቀድ የጀመረች ይመስል ነበር። እንደምሄድ ተስፋ እያደረገች ነበር።

በቀጣዩ ቀን ማክሰኞ ከስራ በጊዜ ለመመለስ ወሰንኩ። የአበባ ስጦታ ሰጥቼያት ሰርፕራይዝ ላደርጋት ፈልጌ ነበር። እና ቀያይ ሮዝ አበባዎችን ገዛሁ። እሷ የምትወዳቸው አበቦች ነበሩ።

ቀስ ብዬ በሩን ከፈትኩኝ። በእኔ ቤት ድንገት ሰርፕራይዝ ላደርጋት ነበር ሀሳቤ። በሩን ስከፍት አልሰማችኝም። ወደ ሳሎን አመራሁ። ሳራ ከመስኮቱ አጠገብ ቆማለች። ስልክ እያናገረች ነበር። በለሰለሰና ዝቅ ባለ ድምፅ ከሆነ ሰው ጋር ታወራለች። በጣም ጣፋጭ በሆነ ድምፅ፣ ልክ ያኔ ስንተዋወቅ ከእኔ ጋር በምታወራበት አይነት ድምፅ። 

"በጣም ቸኩያለሁ።" በስልኩ አፍ አንሾካሾች። "ትላንት ነው የነገረኝ... በቅርቡ ሊሄድ ነው... አዎ ቢያንስ ከሁለት ሳምንት በፊት ላይመለስ ይችላል... ሙሉ ሳምንቱን... እኛ ብቻ"

ልቤ መምታቱን አቆመ። በእጄ የያዝኳቸው አበባዎች እንደ ብረት ከበዱኝ። በመሀል ሳራ ዞር ዞር አለች። አየችኝ። ስልኳ ከእጇ ላይ ተንሸራቶ ሶፋው ላይ ወደቀ።"

"ዴቭ አስደነገጥከኝ!" ብላ ጮኸች። በጣም የተረበሸች ትመስል ነበር። 

"ከማን ጋር ነበር እያወራሽ የነበረው?" ጠየኳት። ድምፄ ለራሴ ጆሮ እንግዳ መስሎ ተሰማኝ።

"ከእህቴ ጋር" አለች ፈጠን ብላ። በጣም ፈጠን ብላ። "ከእህቴ ጋር ነበር ሳወራ የነበረው።" 

እህቷ አውስትራልያ ነው የምትኖረው። አሁን በአውስትራልያ ሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ነው። እህቷ በዚህ ሰዓት ከመተኛት ውጪ ሌላ ምንም ልታደርግ አትችልም።  እየዋሸች እንደነበር አውቂያለሁ። ግን ፈርቼ ነበር። እውነታውን መጋፈጥ ፈራሁ። እና እንደ ፈሪ ሆንኩኝ። 

"እንቺ" አልኳት አበባዎችን እየሰጠኋት። "ላንቺ ነው"

ተቀበለችኝ። "አመሰግናለሁ" አለች። ወደ እኔ ግን አላየችም።

ከሁለት ቀናት በኋላ ማለትም ሐሙስ ቀን..  ጠዋት ላይ አለቃዬ ደወለልኝና ወደ ቢሮው እንድመጣ ነገረኝ። ሔድኩ። "ዳዊት መሄድህ ግድ ነው።" አለኝ። "በረራህ ቡክ ተደርጓል። ነገ ጠዋት ትሔዳለህ።" 

ለጉዞዬ ለመዘጋጀት ወደ ቤት ሄድኩኝ። ሳራ ቤት ነበረች። መሔዴ ግድ እንደሆነ ስነግራት ታዝናለች ብዬ ነበር። ከዚያ ይልቅ ግን አይኖቿ ሲፈኩ ተመለከትኩ። 

"ቺካጎ ምቹ ከተማ ናት።" አለችኝ ልክ ቺካጎን ከዚህ በፊት እንደማላውቃት ነገር።

ሻንጣዬን በማዘጋጀቱ አገዘችኝ። ቲሸርቶቼን በሻንጣው ውስጥ እየከተተች የሆነ ዘፈን ለራሷ ታንጎራጉር ነበር። ለወራቶች ርቋት የነበረው ደስታዋ ተመለሰ። ልሄድ በመሆኑ በጣም ደስተኛ ነበረች። ለምን እንደሆነ ግን ግራ ገባኝ። ማሰብ የማልፈልጋቸው ሀሳቦች በአዕምሮዬ መርመስመስ ጀመሩ። 

ያን ቀን ምሽት እንቅልፍ መተኛት አልቻልኩም። የመኝታ ክፍላችን ኮርኒስ ላይ እንዳፈጠጥኩ በሀሳብ ጭልጥ አልኩ። ከጎኔ የተኛችውን ሳራን ትንፋሽ እያዳመጥኩ ሌሊቱ ነጎደ።

ድንገት አንድ አደገኛ እቅድ አቀድኩኝ። ግን እቅዴ ስለሚያመጣው ችግር በደንብ አላሰብኩበትም። ያበደ ሰው ካልሆነ በስተቀር ይህንን እቅድ ማንም ሊያቅደው አይችልም። የሚያሳምም እቅድ ነበር። ግን ማወቅ ነበረብኝ። ሁሉንም እውነት በራሴ አይኖች ማየት ነበረብኝ።

እቅዴን እንዴት መፈፀም እንዳለብኝ እያሰብኩ አርብ ጠዋት መጣ። ልክ ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት ሲል አአስቀድሜ የደወልኩለት ታክሲ እኔን ለመውሰድ ከቤቴ ተገኘ። 

"መልካም መንገድ ይሁንልህ" አለች ሳራ የአጥሩ በር ላይ እንደቆመች። ጉንጬን ሳመችኝ። ከንፈሮቿ ደረቅና ቀዝቃዛ ነበሩ። "እንደደረስክ ደውልልኝ" 

"አፈቅርሻለሁ" አልኳት። አይኖቿን በጥልቀት አየኋቸው። በአይኖቿ ውስጥ የድሮዋን ሚስቴን እየፈለኩ ነበር። እስከ መቼውም ድረስ ላትጠላኝ ቃል የገባችልኝን ሚስቴን እየፈለኩ ነበር። ግን አጣኋት። "እኔም እወድሃለው!" የሚለውን ምላሽ ለመስጠት እንኳን ከበዳት።

"አውቃለሁ" አለችና የአጥሩን በሩን ዘጋችው። 

ወደ ታክሲው ገባሁ። "ወደ ኤርፖርት ነው የምንሔደው" አልኩት ባለታክሲውን ድምፄን ከፍ አድርጌ ሳራ እንዲሰማት። ይህ የእቅዴ የመጀመርያ እርምጃ ነበር። 

ለአስር ደቂቃዎች ያህል ተጓዝን። ልቤ ልክ እንደ ከበሮ እየደለቀ ነው። የእጄ መዳፎች በላብ ረጥበዋል። 

"አቁም፣" አልኩት ሹፌሩን። "ዙርና ወደ ኋላ ተመለስ።" 

ባለታክሲው በኋላ መስታወቱ በኩል ግራ በመጋባት በጥያቄ አይን ተመለከተኝ። "ፓስፖርትህን ረሳህ እንዴ?" 

"ፓስፖርት ሳይሆን ሌላ ነገር ነው የረሳሁት" አልኩት። "ቤቴ ከመድረስህ ሁለት ቅያስ በፊት ታወርደኛለህ።" 

ሹፌሩ እንዳልኩት አደረገ። ከፈልኩትና ወረድኩኝ። የጠዋቱ ብርድ አጥንቴን ዘልቆ ሲገባ ታወቀኝ። ቀዝቃዛው ነፋስ ፊቴን ገረፈኝ። ሻንጣዬን በእጄ እየጎተትኩኝ በእግረኛው መንገድ ላይ መራመድ ጀመርኩኝ። የሚሰማኝ ስሜት የህመም ያህል ነበር። 

በጎረቤታችን አጥር በኩል አድርጌ ማንም ሳያየኝ በኋላው የቤታችን አጥር ዘልዬ ወደ ውስጥ ገባሁ። ወንጀለኛ የሆንኩ ያህል ተሰማኝ። ወደ ራሴ ህይወት ያለማንም ፈቃድ ሰብሬ የምገባ ወንጀለኛ።

ከአትክልት ስፍራው ጀርባ ወደሚገኘው የእንግዶች ማረፊያ ቤት በፍጥነት ሮጥኩኝ። መክፈቻ ቁልፉን ጠዋት በኪሴ ይዤ ነበር የወጣሁት። ወዲያኑ ከፍቼ ወደ ውስጥ ገባሁና ከውስጥ ቆለፍኩት።

የእንግዳ መቀበያ ቤቱ በጣም ተዝረክርኳል። ጠረኑ በጣም ይረብሻል። ይህንን ቤት ለረጅም ጊዜ አልተጠቀምንበትም። ግን አሁን ላቀድኩት እቅድ በጣም ወሳኝ ሆኖ አገኘሁት። መስኮቱ ከዋናው ቤታችን ጋር ትይዩ ነው። ከዚህ ሁሉንም ማየት እችላለሁ። ኪችኑን ማየት እችላለሁ። ዋናውን ሳሎን ማየት እችላለሁ። በመስታወት በተሰራው በር በኩል ደግሞ በረንዳችንን በደንብ መመልከት እችላለሁ። እና በሁለተኛው ፎቅ ላይ የሚገኘውን የመኝታ ቤታችንን መስኮት በግልፅ ያሳየኝ ነበር።

ሻንጣዬን አስቀመጥኩ። ከመስኮቱ አጠገብ ካለው ወንበር ላይ ቁጭ አልኩኝ። ሳራ እንዳትጠረጥር የክፍሉን መብራቶች አላበራሁም። 

መጠባበቅ ጀመርኩኝ... ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ሆነ። ቤቱ ጭር እንዳለ ነው።

ከጠዋቱ 2:30...

ሳራ ወደ በረንዳው ወጣች። የሌሊት ልብሷን ለብሳለች። ይህንን የሌሊት ልብስ ከዚህ በፊት አላየሁትም። አጭርና ቀይ ነው። በጣም በውድ ዋጋ እንደገዛችው ያስታውቃል። እጆቿን አሳስባ ሰውነቷን ካንጠራራች በኋላ ወደ ሰማዩ ተመለከተች። ፈገግ አለች። ፈገግታዋ በነፃነት የተገኘ ነበር የሚመስለው።

ወደ ውስጥ ተመልሳ ገባች። በበሩ በኩል አድርጌ ኪችን ውስጥ ስትንቀሳቀስ አየኋት። እያፀዳች ነበር። የምታፀዳው ግን የኪችኑን ቆሻሻ አልነበረም። ቤቱን ለተለየ አላማዋ እያዘጋጀች ይመስላል።

ከዚያም እቃዎችን ማንቀሳቀስ ጀመረች። የእኔን እቃወች። የእኔን ፖስታዎችና አንዳንድ ወረቀቶች ወደ ቁም ሳጥኑ ውስጥ ስትከታቸው ተመለከትኳት። "ምርጡ አርክቴክት" የሚል ፅሁፍ የታተመባትንና በተለየ ዲዛይን የተሰራችውን የቡና መጠጫዬን ወደ እቃ ማጠቢያው ውስጥ አስገባችው። የተዝረከረኩትን ልብሶቼን ሰብስባ ወደ ውስጥ ደበቀች።

እኔን እና የኔን ነገሮች መሰረዝ የፈለገች ትመስላለች። እኔ እዛ ቤት ውስጥ እንደምኖር የሚያሳብቁ መረጃዎችን በሙሉ በተቻላት አቅም ሁሉ ለማጥፋት ሞከረች። ግን ለምን? ልቤን እንደውጋት ነገር ተሰማኝ። የመጫጫን አይነት ስሜት። የሆነ ሰው ደረቴ ላይ እግሩን የጫነብኝ ያህል እስኪሰማኝ ድረስ።

አራት ሰዓት ሆነ። 

አንድ መኪና ወደ ቤታችን የጀርባ በር አቅራቢያ ድምፅ አሰማ። ሆዴ መገለባበጥ ጀመረ። ጊዜው የደረሰ መሰለኝ። ከእውነቱ ጋር የምጋፈጥበት ጊዜ። ወደ ኋላ በር ተመለከትኩኝ። በሩ ከመንኳኳቱ በፊት ሳራ በፍጥነት ከፈተችው። 

አንድ ሰው ወደ ውስጥ ገባ። ረጅም ነው። ደረቱ ሰፊ። ሰማያዊ ጅንስና ከሰውነቱ ጋር የተጣበቀ ጥቁር ቲሸርት ለብሷል። የጂም ቦርሳ የሚመስል ነገር በትክሻው አንጠልጥሏል።

ትኩረት ሰጥቼ ስመለከተው ደሜ ቀጥ አለ። ሰውዬው እንግዳ አልነበረም። ከጂም የመጣ ተራ ሰውም አልነበረም። ማርቆስ ነበር። ጓደኛዬ! 

ማርቆስ ከኮሌጅ ጀምሮ የማውቀው የልብ ጓደኛዬ ነው። በየሳምንቱ መጨረሻ ላይ አብረን ኳስ እንጫወታለን። በእኔና በሳራ ግብዣዎች ላይ ተገኝቷል። በአንድ ጠረጴዛ ላይ አብሮኝ ተቀምጧል። የምበላውን በልቷል። የምጠጣውን ጠጥቷል። እጄን ጨብጦ ሰላም እያለኝ "ወንድሜ" ብሎ ጠርቶኛል።

አየኋቸው። ባለማመን። 

ሳራ ዘለለችና አንገቱ ላይ ተጠመጠመች። እግሮቿን አንስታ በጀርባው ላይ አቆላለፈቻቸው። ማርቆስ ሻንጣውን ጣለና ከንፈሩን ከከንፈሮቿ አጣበቃቸው። ሳማት። አሳሳሙ ልክ እንደራበው አይነት ይመስል ነበር። ዝም ብሎ መሳም አልነበረም። በስሜት የተሞላ ነበር።

እነሱን ማየት ቀፈፈኝ። አመመኝ። ሊያስታውከኝ ጉሮሮዬን ተናነቀኝ። 

ማርቆስ፣ ጓደኛዬ። ሳራ ሚስቴ።

ተያይዘው ወደ ኪችኑ ገቡ። ሳራ በጣም እየሳቀች ነበር። ፊቱን ዳበሰችው። ክንዱን ዳበሰችው። በአድናቆትና በናፍቆት ተመለከተችው። "ምን ያህል ቢናፍቃት ነው?" ስል ራሴን ጠየኩ። 

ቡና አፈላችና በሌላ ስኒ ቀዳችለት። የእኔ ስኒ እንደተደበቀ ነው። 

በጨለማው የእንግዳ ክፍል ውስጥ ተቀምጬ ቀረሁ። መንቀጥቀጥ ጀመሪያለሁ። ሮጬ መውጣት ፈለኩ። ሮጬ ወጥቼ የማርቆስን ፊት በቦክስ መጠርመስ፣ ሆዱንም በሽጉት መቅደድ አማረኝ።

ግን ቆየሁ። ሁሉንም ማየት ነበረብኝ። 

ከጥቂት ቆይታ በኋላ እቃዎችን ማጓጓዝ ጀመሩ። ማርቆስ ወደ መኪናው ተመልሶ ሔደ። የመኪናውን ኮፈን ከፍቶ ሁለት ትልልቅ ተጨማሪ ሻንጣዎችን አመጣ። ቀጠሯቸው የአንድ ቀን ብቻ አልነበረም። እኔ ከቺካጎ እስክመለስ ድረስ አብረው ለመሆን አቅደዋል። በእነሱ ሀሳብ እኔ ቢያንስ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ቺካጎ ውስጥ ስለምቆይ ብዙ ጊዜ ይኖራቸዋል።

ወደላይኛው ፎቅ ሲወጡ አየኋቸው። ከዚያም ወደ መኝታ ክፍላችን። ማርቆስ ልክ ቤቱ የእሱ እንደሆነ ሁሉ በክፍሉ ውስጥ መንጎራደድ ጀመረ። ወደ አልጋው ተመለከተ። ተቀመጠበት። ከዚያም በጀርባው ጋደም ብሎ ምን ያህል ምቹ እንደሆነ ለማየት ሞከረ። 

ቀጥሎ ሳራ ውስጤን ዘልቆ የወጋኝን አንድ ነገር አደረገች። ከአልጋው ጎን ካለው ጠረጴዛ ላይ በፍሬም የተሰራው በሰርጋችን እለት የተነሳነው ፎቶ ነበር። ፎቶው ላይ ደስተኞች ሆነን እንታያለን። በፍቅር ነበር የማያት። ሳራ ፎቶውን አነሳችው። ለአፍታ ተመለከተችው። ከዚያም የጠረጴዛውን መሳቢያ ከፍታ ፎቶውን ወደ ውስጥ ወረወረችውና መሳቢያውን በሀይል ገፍታ ዘጋችው።

ጠረጴዛው ላይ በፎቶው ምትክ ወይን የያዘ ጠርሙስ አስቀመጠች። ማርቆስ ሳቀ። ከኋላዋ መጣና አንገቷ ላይ ሳማት።

ሻንጣዎቹን መክፈትና በውስጡ ያሉትን ልብሶቹን ማውጣት ጀመሩ። ቲሸርቶቹን በእኔ ቁምሳጥን ውስጥ አንጠለጠላቸው። የጥርስ ብሩሹን በመታጠቢያ ክፍል ውስጥ አስቀመጠ። እኔ ለቀናት ነበር ወደ ቺካጎ ልሄድ የነበረው። እነሱ ግን የልጅነታቸውን እቃ እቃ መጫወት ፈለጉ። ልክ እኔ እዚህ ምድር ላይ እንደሌለሁ ቆጠሩኝ። 

ቀኑን ሙሉ በእንግዳ መረፊያ ክፍሉ ውስጥ ተቀመጥኩ። ምንም አልበላሁም። ምንም አልጠጣሁም። የሁለቱም ከሃዲዎች እንቅስቃሴ ከማየት በስተቀር።

ኪችን ውስጥ ምሳ አብረው ሲሰሩ አየኋቸው። ዱቄት እርስ በእርስ ሲረጫጩ እየኋቸው። ከስቶቩ አጠገብ ቆመው ከንፈር ለከንፈር ሲቃመሱ አየኋቸው። ሳራ ከዚህ በፊት እኔ ኪችን ውስጥ አብሪያት እንድሆን አትፈልግም ነበር። የእኔን ከእሷ ጋር ኪችን ውስጥ መገኘት ልክ እንደ ነውር ነበር የምትቆጥረው። ግን ከእሱ ጋር ሲሆን ነውሩ ክብር  ሆነላት።

ምሽቱ መጣ። ፀሐይ አዘቀዘቀች። በዋናው ቤት ውስጥ ያሉት መብራቶች በሩ።

በሳሎን ውስጥ ሶፋ ላይ ቁጭ ብለዋል። ፊልም ማየት ጀመሩ። እና ፊልሙ ተጀምሮ እስከሚያልቅ ሳራ ጭንቅላቷን በማርቆስ ደረት ላይ አስደግፋ ነበር። እውነተኛ ጥንዶች ነበር የሚመስሉት። ቤቱም የእነሱ ነበር የሚመስለው። እኔ በተቃራኒው የእነሱን ፍቅር ለመረበሽ አጥራቸውን የሰበርኩ ወንጀለኛ።

ግንኙነታችው የመጀመርያ እንዳልነበር ተረዳሁ። ማንም ሰው በመጀመርያ ቀኑ ብቻ በሙሉ የራስ መተማመን እንዲህ ወደ ሰው ቤት መኝታ ክፍል ሊገባ አይችልም። ለረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነት ከሌላቸው በስተቀር። ግን ምን ያህል ጊዜ? ወራት? አመታት? መቼ ነው ከጀርባዬ ሆነው በህይወቴ ሜላገጥ የጀመሩት? ለመኪናዋ መግዣ የሚሆን ብር ለማግኘት ለማግኘት በስራ ተጨናንቄ እያለ? ወይስ የመጀመርያ አመት የጋብቻ አንቨርሰሪያችንን እንዴት ማክበር እንዳለብን እቅድ በማውጣት ላይ እያለሁ?

ከምሽቱ 4 ሰዓት ሆነ። የታችኛው ፎቅ መብራቶች ጠፉ። የመኝታ ክፍላችን መብራቶች እንደበሩ ናቸው። ግን ሳራ የክፍሉን መስኮቶች መጋረጃ ዘረጋቻቸው። አሁን ብርሃኑ ባረፈባቸው የመስኮቱ መጋረጃዎች ላይ የሚንቀሳቀሱ ጥላዎች ብቻ ናቸው የሚታዩኝ። የሚስቴና የልብ ጓደኛዬ ጥላዎች።

በጨለማው የእንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ እንደተቀመጥኩ ቀረሁ። ከመጋረጃዎቹ ጀርባ ምን እየተፈጠረ እንደሆነ አሰብኩ። የምወዳት ሴት ልክ ለእኔ በጆሮዎቼ ስታንሾካሹክልኝ የነበሩትን ቃላት ለልብ ጓደኛዬ ስታንሾካሹካቸው በህሊናዬ ታየኝ። የፈረስ ጭን ከሚያክለው ደረቱ ላይ ተለጥፋ ... አለቀስኩ።

ትልቅ ሰው ነኝ አውቃለሁ። ብዙውን ጊዜ አላለቅስም። ግን ያን ቀን ምሽት በተዝረከረከው የእንግዳ መቀበያ ውስጥ ቁጭ ብዬ አይኖቼን እስኪቀሉ ድረስ አለቀስኩ። ትዳሬ ስለሞተ አለቀስኩ። ምርጡን ጓደኛዬን ስላጣሁት አለቀስኩ። የምወዳት ሴት ለአመታት ስትወደኝ እያስመሰለች እንደነበር እያሰብኩ አለቀስኩ። ሞኝ ለነበርኩባቸው ጊዜያት አለቀስኩ። 

ሌሊቱን ሙሉ ምንም እንቅልፍ አልወሰደኝም። ወደ መኝታ ክፍሉ መስኮቶች እንዳፈጠጥኩኝ ሌሊቱ ነጋ። 

ከዚያም ቅዳሜ ቀን እንደምንም መጣ። ፀሐዮዋ ወርቃማ ጨረሮቿን መርጨት ጀመረች። ወፎች መዝፈን ጀመሩ። ተፈጥሮ ውብ እንደሆነች ነቃች። እኔ ግን ከነስብራቴ እንቅልፍ እንኳን ባይኔ ሳይዞር ሌሊቱ ነጋ። እና እኔ አዝኜ ተፈጥሮ ማማሯ ተገቢ እንዳልሆነ ተሰማኝ። ተፈጥሮ በእኔ ላይ የምታላግጥብኝ መሰለኝ። 

ጠዋት 3 ሰዓት ሲሆን ቁርስ ለመብላት ወደ በረንዳው ወጡ። ያለሁበትን የእንግዳ ማረፊያ ቤት መስኮት በትንሹ ከፈትኩት። ነፋሱ ወደ እኔ አቅጣጫ እየነፈሰ ነው። ምን እንደሚያወሩ ልሰማቸው ፈለኩ። ቀለል ያለ ነገር ነበር የሚበሉት። ሌሊታቸው ምቹ እንደነበር ከፊታቸው ላይ በግልፅ ይታያል። በጣም ዘና ያሉ ይመስላሉ። ሀጢያት ሳይሆን ጀብዱ የፈፀሙ ያህል ድፕስተኛ ሆነዋል።

"ህይወት እንዲህ ነው" አለ ማርቆስ። ከዚያም እጆቹን ወደ ላይ ወጥሮ ሰውነቱን አንጠራራ። "ዳዊት ጥሩ ቤት አለው።" 

ደሜ ሲሞቅ ተሰማኝ።

"በቅርቡ የእኔ እና ያንተ ብቻ ይሆናል።" አለች ሳራ።

ደነዘዝኩ። ምንድነው ያለችው?

"ስለግንኙነታችን የጠረጠረው ነገር ያለ ይመስልሻል?" ማርቆስ ጠየቃት ከሚበሉት ቁርስ ላይ አንድ ጉርሻ እየጎረሰ።

"አይ" ሳራ ሳቀች። ሳቋ አስጠላኝ። "ዳዊት እውር ነው። እሱ የሚታየው ስራው ብቻ ነው። ጥሩ ሚስት እንደሆንኩለ ነው የሚያስበው። ስለሁለታችን ምንም ሀሳቡ የለውም።"

"መቼ ልትነግሪው ነው?" ማርቆስ ጠየቀ።

"መቼም አልነግረውም።" አለች። ከዚያም የብርቱካን ጭማቂዋን አንድ ጉዜ ማገች። "የፍቺ ወረቀት በቀጣይ ወር አስገባለሁ። መጀመርያ ግን አንድ የምጠብቀው ገንዘብ አለ። ይህ ገንዘብ በእጄ እንደሚገባ ማረጋገጥ አለብኝ። በዚህ አመት በጣም አሪፍ ቦነስ ያገኛል። የቦነሱን ግማሽ ደግሞ እንደ ሚስትነቴ ማግኘት አለብኝ ብዬ አምናለሁ።" የሚያስጠላ ሳቋን ቀጠለች።  

"በጣም ክፉ ነሽ።" አለና ማርቆስ አብሯት ሳቀ። "እምነትሽን ወድጄዋለሁ።" 

"ዳዊት ማለት አሰልቺ ሰው ነው ማርቆስ" አለች። "በጣም ሲበዛ አሰልቺ ሰው ነው። ሁሉም ወሬዎቹ ስለ አርክቴክቸርና ስለሚሰራቸው የቤት ዲዛይኖች ነው። አንተ ግን... አንተ ግን በጣም ነው የምታነቃቃኝ። በህይወት እንዳለሁ የሚሰማኝ ከአንተ ጋር ስሆን ነው።" 

"እና ቤቱን በተመለከተ ምን ልታደርጊ ነው?" ማርቆስ ጠየቃት።

"ቤቱን አገኘዋለሁ። የእኔ ይሆናል።" አለች በሙሉ የራስ መተማመን ስሜት። "ጥሩ ጠበቃ አለኝ። ከእሱ ጋር ሆኜ ዳዊትን ከጨዋታ ውጪ አደርገዋለሁ። እና ያን ጊዜ ወደዚህ የምትመጣው በቋሚነት ከእኔ ጋር ለመኖር ነው። ባሌ ለመሆን።"

የጁስ ብርጭቆዎቻቸውን አጋጩ። እኔን ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ ፅዋቸውን አነሱ። 

እስኪበቃኝ ሰማኋቸው። 

የእንግዳ ማረፊያ ቤቱን መስታወት ዘጋሁና ከተቀመጥኩበት ተነሳሁ። ብዙ ሰዓታትን መቀመጤ የታወቀኝ እግሮቼ ለአፍታ አልንቀሳቀስልህ ሲሉኝ ነበር። አይኖቼ ከእንቅልፍ እጦት በላይ ባዩት ነገር ደም ለብሰዋል። ግን አሁን ሀዘኔ የለም። እንባዬም ደርቋል። አሁን ንዴት ብቻ ነው ከእኔ ጋር የቀረው። የቀዘቀዘ፣ ግን የጠነከረ ንዴት። ቤቴን ሊወስዱ ፈለጉ? ገንዘቤን ሊወስዱ ፈለጉ? እንደ እውር ቆጠሩኝ? እምነቴን የወሰዱት ከእነዚህ ሁሉ እንደሚበልጥ ብነግራቸው ደስ ባለኝ ነበር። 

"አሳያቸዋለሁ" አልኩ ለራሴ።

ስልኬን ቼክ አደረኩ። ንግግራቸውን በሙሉ ቀድቼው ነበር። በቪዲዮ ነበር እየቀረፅኳቸው የነበረው። በእጄ መንቀጥቀጥ ምክንያት ቪዲዮው ትንሽ ጥራት ቢጎለውም ድምፃቸው ግን በደንብ ይሰማ ነበር። 

"አሰልቺ ነው።"  ... "ቤቱን አገኘዋለሁ።" ... "ስለ ግንኙነታችን ምንም ሀሳቡ የለውም።"  የሚያስፈልጉኝ ሁሉም ነገሮችን ይዣለሁ።

የእንግዳ ማረፊያ ቤቱን በር ከፈትኩና ከፈካችው ፀሀይ ጋር ተያየሁ። ወደ ከሃዲ ወዳጆቼ ጉዞዬን ጀመርኩ። በዚህ ሰዓት በቀስታ አልነበረም የምጓዘው። ኮቴዬን እያሰማሁ ፣ የደረቁጥትን የዛፍ ቅጠሎችንና ሳሮችን ያለ ሰቀቀን እየረገጥኩ ነበር። 

ወደ በረንዳው ተጠጋሁ። ሁለቱ ከሃዲ ወዳጆቼ አሁንም ይሳሳቃሉ። ሳራ በአንድ እጇ በያዘችው ማንኪያ የሚበላ ነገር ወደ አፏ እየከተተች፣ አንድ እጇን ደግሞ የማርቆስ ጉልበት ላይ አርጋ አይን አይኑን እያየች ከከንፈሩ የሚፈሱትን ቃላት በጆሮዎቿ ትለቅማለች። 

አጠገባቸው ደረስኩ። 

"እንደምን አደራችሁ?" አልኩ። ድምፄን እንደሰሙ ወዲያው ሳቃቸውና ድምፃቸው ጠፋ። ሳራ የያዘችው ማንኪያ ከእጇ ላይ ወደቀና ጠረጴዛው ላይ ካሉት ሳህኖች ጋር ተጋጨ። ፊቷ በአንድ ጊዜ ገረጣ። ገረጣ ብቻ ሳይሆን እንደ ወረቀት ነጭ ሆነ።

ማርቆስ ከመቀመጫው በፍጥነት ብድግ ብሎ ቆመ። ከመደንገጡ የተነሳ ጠረጴዛውን ለጥቂት ገልብጦት ነበር። "ዳዊት?!" ተንቀጠቀጠ። "ጓደኛዬ ... እኔ..." አላስጨረስኩትም። በፊት እጄን ጨብጦ "ወንድሜ" እንዳለኝ ሁሉ አሁንም "ጓደኛዬ" ብሎ ሊዋሸኝ ፈልገ።

"ተቀመጥ ማርቆስ" አልኩት በተረጋጋ ስሜት። ድምፄ ላይም ምንም ቁጡነት አልነበረም። በዚህ ደረጃ መረጋጋቴ ለራሴም ገረመኝ። 

ሳራ ተነሳች። እሷም እንደ እሱ እየተብረከረከች "ዳዊት... ወደ... ወደ ችካጎ ... ቺካጎ ሃደህ ነበር አደል? እንዴት እዚህ ልትሆን ቻልክ? ሁሉም ነገር ሰላም ነው?" አለች።

"አይ አይደለም ሳራ" አልኩ። "ቺካጎ አልነበርኩም። ከትናትን ጠዋት ጀምሮ በእንግዳ ማረፊያ ቤት ውስጥ ነበርኩኝ። አይኖቿ ፈጠጡ። ወደ እንግዳ ማረፊያ ቤቱ ተመለከተች። ከዚያም ወደ እኔ ተመልሳ አየች። እና ሂሳቡን ሰራችው። እያየኋቸው እንደነበረ ገባት።

"እያየኸን ነበር?" ስትል ጠየቀችኝ በሹክሹክታ።

"ሁሉንም ነገር አይቻለሁ።" አልኳት። "በር ከፍተሽ ወደ ቤት ስታስገቢው አይቻለሁ። የሰርጋችንን ፎቶ ወደ መሳቢያው ውስጥ ስትደብቂው አይቻለሁ። የጓደኛዬን ወገብ በጭኖችሽ ጨምቀሽ ይዘሽ ከንፈርሽን ሲስምሽ አይቻለሁ። የመኝታ ቤታችን መጋረጃዎች ላይ ሁለት ጥላዎች ሲንቀሳቀሱ ... ሁሉንም ነገር አይቻለሁ።" 

ማርቆስ ወደ መሬት ማየት ጀመረ። አይኖቼን ለማየት አልቻለም። ግን አሁንም እኔን እንደ እውር መቁጠሩን አላቆመም። ያየሁትን የምክድ ጅል አርጎ ቆጠረኝ። "ዳዊት ስማኝ... አንተ እንዳሰብከው አይደለም..." 

"አፍህን ዝጋ!" አልኩት። "አሁንም እውር እንደሆንኩ ነው የምታስበው?! ሁሉም ነገር እንዳሰብኩት ነው። ምንም ለማስተባበል እንዳትሞክር!"

ወደ ሳራ ዞርኩ። "እና አንቺ... ያልሽውን ሁሉንም ነገር ሰምቻለሁ። የእኔን ቦነስ መጋራት ፈለክሽ? ቤቴን መውሰድ ፈለክሽ? እና እኔ አሰልቺ እንደሆንኩ ነው የምታስቢው?" 

ማልቀስ ጀመረች። ግን እንባዋ የአዞ እንባ ነበር። 

"ዳዊት እባክህ" ሲቃ ተናነቃት። የውሸት ሲቃ!። " ግራ ተጋብቼ ነበር። ስህተት ሰርቻለሁ። እባክህ የእኔ ፍቅር ይቅርታ አርግልኝና አንዴ ተቀምጠን እናውራ።"

እጄቼን ለመያዝ ሞከረች። ወደ ኋላ ሸሸኋት። "እንዳትነኪኝ!" 

"ዳዊት አፈቅርሃው" ዋሸች አሁንም። "ማርቆስ ለእኔ ምኔም አይደለም። ለጊዜያዊ ደስታ ብቻ ነው። እባክህ..." 

"ጊዜያዊ?" በጣም ሳኩኝ። አሳሳቄ ለእኔም እንግዳና የሚያስጠላ ነበር። "ሁለት ትልልቅ ሻንጣዎቹን ይዞ የመጣው ለጊዜያዊ ደስታ ብቻ ነው? እኔን ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ ስታወሩ ነበር። ህይወቴን ለመስረቅ እቅድ ስታወጡ ነበር።"

"አዎ በቃ!" ድንገት ጮኸች። "አዎ! ሰልችተኸኛል። ሁልጊዜ የምታወራው ስለስራ ብቻ ነው። ከእኔ ጋር ሆነህ አታውቅም። እኔ ደግሞ ደስታን የሚሰጠኝ ሰው እፈልጋለሁ።"

"መልካም" አልኩ። "አሁን ደስታን የሚሰጥሽ ሰው አግኝተሻል። ምርጡ ጓደኛዬ ምርጥ ደስታን ይሰጥሻል።"

የእጅ ሰዓቴን ተመለከትኩና "አንድ ሰዓት ብቻ አላችሁ።" አልኳቸው።

"ምን?" አለ ማርቆስ።

"አንድ ሰዓት" ደከምኩለት። "ሁለታችሁም ሻንጣችሁን ያዙና ከቤቴ ውጡ።" 

"እኔን በፍፁም ማባረር አትችልም!" አለች ሳራ። "ይህ የአንተ ብቻ ሳይሆን የእኔም ቤት ነው።" ድምጿ ውስጥ እልህ ተሰማኝ።

ይህን ጊዜ ስልኬን አወጣሁና የቅጂውን ማጫዋቻ ተጫንኩት።  "ዳዊት አሰልቺ ሰው ነው... ቤቱን አገኘዋለሁ... ያኔ አንተ የምትመጣው በቋሚነት ከእኔ ጋር ለመኖር ነው።" 

ከስልኩ የሚወጣው ድምጿ ወደ አትክልቶቹ እስከሚያስተጋባ ድረስ ተሰማ። አፏን ከፍታ ቀረች። መረጃ የያዝኩባት አልመሰላትም ነበር። 

"በእርግጥ" አልኩ። "ከትዳር ውጪ እንደማገጥሽብኝ የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ እስካለኝ ድረስ ለእኔ የፍርድቤቱ ጨዋታ በጣም ቀላልና ውጤቱም አሩፍ ነው የሚሆንልኝ። ግን ለአሁን ከዚህ ቤት በፍጥነት እንድትወጡ እፈልጋለሁ። የማትወጡ ከሆነ ወደ ፖሊስ ደውዬ ቪዲዮዋችሁን ለማሳየት እገደዳለሁ።"

"ማርቆስ የሆነ ነገር አርግ እባክህ" ሳራ ወደ ማርቆስ አፈጠጠች። ምን እንዲያደርግ እንደፈለገች ገብቶኛል። ጡንቻውንና ጉልበቱን ተጠቅሞ የቪዲዮ ማስረጃውን ከነስልኬ እንዲቀበለኝ ነው ሀሳቧ። ምናልባት አልሰጥም ብዬ የማስቸግር ከሆነም እንዲገለኝ። 

ግን ሞኝ አልነበርኩም። ማርቆስ ሀሳቧን ለመፈፀም እያሰበ ወደ እኔ ማየት ጀመረ። ምንም ቃል አልተናገርኩም። ጃኬቴን ከፈት አርጌ በቀበቶዬ ስር የሸጎጥኩትን አነስተኛ ሽጉጥ አሳየሁትና "ቅምጥህን ይዘህ ቶሎ ከዚህ ብትሔድ ይሻልሃል!" አልኩት። ማርቆስ ሽጉጡን ሲያይ ፈራ። 

"ሳራ ነይ" አለ። "እንሂድ። አሁን ምንም ማድረግ የለብንም። ሁሉንም በፍርድ ቤት ትጨርሻለሽ።" ሳራ የማርቆስን መፍራት ስትመለከት ግራ ተጋባች። እሱ ያየውን ያየች አልመሰለኝም።

ማርቆስ ሻንጣዎቹን ሊያወጣ ወደ ውስጥ ገባ። ሳራ ተከተለችው። እኔ በረንዳው ላይ እንደቆምኩ አየኋቸው። አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለቱም ሻንጥልዎቻቸውን ይዘው ወደታችኛው ወለል ወረዱ። ሳራ ልብሶቿን ብቻ ነበር የያዘችው። ከመውጣቷ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ አየችኝ። ግን አይኖቿ ላይ የፍርሃት ስሜት አላየሁም። የጥላቻ የእልህና የንዴት ስሜቶች ተደበላልቀው ነው ያስተዋልኩት።

"ከዚህ በኋላ ብቻህን ትሆናለህ።" አለችኝ። "በትልቅ ቤት ውስጥ የተከበብክ ብቸኛና አስፈሪ ሰው ትሆናለህ።" 

"ምናልባት" አልኳት። "ግን ቢያንስ እኔ ለራሴና ለቤቴ ታማኝ ነኝ። እና ከህሊና ፍርድ ነፃ ነኝ።" ንግግሬ የነካት ይመስላል። ምንም ሳትመልስልኝ ሻንጣዋን እየጎተተች ወደ በሩ ሔደች። ማርቆስም እንደተነከሰ ውሻ ከኋላዋ ተከተላት። 

ወደ ማርቆስ መኪና ገቡ። ተከትያቸው ወጣሁና መንገዱ ላይ ቆምኩኝ። መኪናቸውን አስነስተው ጉዞ ጀመሩ። ከእይታዬ እስኪሰወሩ ድረስ ቆየሁና ወደ ቤት ተመለስኩ። 

ወደ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ሁሉንም ክፍሎች ማየት ጀመርኩኝ። ቤቱ በጣም ቆሽሿል። የተራረፉና የተበታተኑ የምግብ ቁርጥራጮች ጠረጴዛው ይታያሉ። ኪችኑ ውስጥ ደግሞ እንደ ህፃን ሲረጫጩት የነበረው ዱቄት ተበታትኗል። 

ወደ መኝታ ቤታችን አመራሁ። ቁም ሳጥኑን ከፈትኩት። የማርቆስ ልብሶች ሽታ አሁንም ድረስ አለ። የእሱ ጠረን ያለባቸውን ሁሉንም ቲሸርቶቼን አወጣሁና አቃጠልኳቸው። አልጋው ላይ የተነጠፉትን ብርድ ልብሶችና አንሶላዎች በሙሉ ቀዳድጄ ጣልኳቸው። ከአልጋችን አጠገብ ያለው መሳቢያ ከፈትኩና ሳራ የደበቀችውን የሰርጋችንን ፎቶ አወጣሁት። ለአፍታ አየሁት። ሁለት ወጣት ጥንዶች። በተስፋ የተሞሉ። ግን ደግሞ በውሸትና በማስመሰል አለም ውስጥ ሲኖሩ የቆዩ ሁለት ወጣቶች። ወደ መኝታ ክፍላችን በረንዳ ወጣሁና ቁልቁል ወረወርኩት። የፍሬሙ መስታወት ወደ አመድነት ተቀየረ። ልክ የእኔ ልብ እንደሆነው።

ከዚያም ወደ እንግዳ ማረፊያ ቤቱ ሔድኩኝና ሻንጣዬን አመጣሁ። 

ያን ቀን ምሽት ቤቱ በጣም ትልቅ ሆነብኝ። ያለመድኩት ዝምታ ድምፅ አውጥቶ በእያንዳንዱ ክፍል አስተጋባ። ልክ ሳራ እንዳለችኝ የብቸኝነት ስሜቱ ከአሁኑ ይፈታተነኝ ጀመር። ግን ሰላማዊ ነበር።

ቀጣዮቹ ጥቂት ወራት በጣም ከባድ ሆነው አለፉ። 

በህይወቴ መቼም ይሆናል ብዬ ከማልጠብቀው ፍቺ ጋር ተጋፈጥኩ። ፍቺ በጣም አስቀያሚ ነገር ነው። ፍቺ ባላቸው ነገር የማይረኩ ሰዎች የሚፈጥሩት የህይወት ጣጣ ነው። ፍቺ የሌላን ሰው ቤት ከመመኘት የሚመጣ ቤት አፍራሽ በሽታ ነው። 

ሳራ ቤቱን ለማግኘት ታገለች። ገንዘቤን ለማግኘት ታገለች። ግን የቪዲዮ ቅጂው በጣም ጠቀመኝ። ስለ እኔ የሚጨነቁ የእኔም የማርቆስም ጓደኞች ከእኔ ጎን ቆሙ። ማርቆስና ሳራ ከእኔ ጀርባ የፈፀሙትን ክህደት እንዳዩ ሁሉም ባለማመን ደንግጠው ነበር። እና ማርቆስን ሙሉ በሙሉ ልክ እንደ እኔ ከህይወታቸው አስወጡት።

ከፍቺ በኋላ እንዴት በድጋሜ የላጤነት ህይወትን መኖር እንዳለብኝ መማር ግድ ሆነብኝ። ምግብ ማብሰል መማር ነበረብኝ። በትልቁ አልጋ መሀል ላይ ለብቻዬ መተኛት ... ሁሉም ነገር ለእኔ በጣም እንግዳ እና ለመልመድ ከባድ ነበር።

የቤቴን በሮች ቁልፍ በጠቅላላ ቀየርኳቸው። የእያንዳንዱን ክፍል ግድግዳ ሌላ ቀለም ቀባኋቸው። አዳዲስ እቃወችን ገዛሁ። እና ሳራን የሚያስታውሱ ነገሮችን አጥፍቼ ቤቴንና ልቤን የራሴ ማድረግ ጀመርኩኝ።

አንዳንዴ የእሷን መኖር የመናፈቅ አባዜ ይጠናወተኛል። አንዳንዴ ቤት ስትመጣ የምቀበላት ወይም ቤት ስመጣ የምትቀበለኝ ነገር ትዝ ይለኝና ያለፉ ጊዜያቶቻችንን እያሰብኩ እናፍቃለሁ። 

ግን ደግሞ ወዲያው የማረፊያ ቤቱን መስኮት አስታውሳለሁ። ለማርቆስ ብላ የለበሰችውን ያንን አጭር ቀይ የሌሊት ልብስ አስታውሳለሁ። የተናገረቻቸውን እያንዳንዱን ንግግር አስታውሳለሁ። "አሰልቺ ነው..."

እና እሷን የመናፈቁ ስሜት ይቆማል። ህይወትን በአዲስ የመጀመር ፍላጎቱ ያድርብኛል።

ከአንድ አመት በኋላ፣ አንድ ቀን ምሽት ላይ በአትክልቱ ስፍራ አትክልቶቹን እያጠጣሁ ነበር። ወይዘሮ አማንዳ የተባለችው አሮጊቷ ጎረቤቴ ጠራችኝ። ስለ እኔና ስለ ሳራ እንዲሁም ስለተፈጠረው ነገር ሁሉ ነግሪያት ነበር። ሁሉንም ነገር ታውቃለች።

"ዳዊት!" አለች። "የአትክልት ስፍራህ በጣም ቆንጆ ሆኗል።" 

"አመሰግናለሁ ወይዘሮ አማንዳ" አልኩና ፈገግ አልኩ።

"አሁን ደስተኛ ትመስላለህ።" አለች። "እንደበፊቱ ፊትህ አይከብድም። ቅልል ብሎሃል።"

መልስ ሳልሰጣት ትንሽ አሰብ አደረኩ። ደስተኛ ሆንኛለሁ? ስል ራሴን ጠየኩት። አዎ! በእርግጥ ደስተኛ ነበርኩ። ግን ሙሉ በሙሉ ደስተኛ አልነበርኩም። አሁንም ልቤ ላይ ብዙ ጠባሳዎች አሉ። ግን በጣም ተረጋግቻለሁ። እውነተኛ ህይወትን እየኖርኩኝ ነው። በውሸት መሰረት ላይ ቤቴን የምሰራ አርክቴክት አልነበርኩም። 

"አዎ አሁን ቀለል ብሎኛል።" አልኳት ወይዘሮ አማንዳን።

ወደ እንግዳ ማረፊያ ቤት ተመለከትኩኝ። ቤቱን አፅድቼዋለሁ። ግድግዳዎቹን ነጣ ያለ ቢጫ ቀለም ቀብቻቸዋለሁ። እና ወደ ስራ መስሪያ ስቱዲዮነት ቀይሬዋለሁ። ከዚህ በኋላ የመደበቂያ ቦታ አይሆንም። ከዚህ በኋላ አዳዲስ ስራዎችን መፍጠሪያ ሆኖ ያገለግላል።

ከራሴ ጋር በድጋሜ ተዋወኩኝ።

ዳዊት እላለሁ። አሁን 36 አመት ሆኖኛል። ፍቺ ፈፅሚያለሁ። ብቸኛ ነኝ። እና ከረጅም ጊዜ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ደህንነት እየተሰማኝ ነው። 

ታሪኬን ስላነበባችሁ አመሰግናለሁ።

ህይወት ልትከብድ ትችላለች። በእርግጥም ትከብዳለች። ሰዎች ሊጎዷችሁ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ በጣም የምትቀርቧቸውና የእኔ የምትሏቸው ወዳጆቻችሁ ልባችሁን ይሰብሩታል። 

ግን ይህንን አስታውሱ። እውነት ምንጊዜም ከውሸት ይሻላል። ብቸኝነት እንዲሰማችሁ ከሚያደርግ ሰው ጋር ከመኖር ከነፃነትና ከእውነት ጋር ለብቻ መኖር በብዙ እጥፍ ይበልጣል። 

ልባችሁን ጠብቁ። ጠንካራ ሁኑ። እና የትኛውም ውድቀትና ክስረት ቡደርስባችሁ ህይወትን ዳግም ከዜሮ ለመጀመር በፍፁም እንዳትፈሩ።


--- አለቀ ---